መፃጉእ

                                                             በመ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የራሷ የሆነ ሥርዓተ አምልኮና ደንብ ያላት ቤተ-ክርስቲያን ናት፡፡ ሥርዓተ አምልኮዋን ከምትፈፅምባቸው መንፈሳዊ መሳሪያዎች መካከል አንዱ ፆም እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በአዋጅ ከደነገገቻቸው አፅዋማት መካከል አሁን እየፆምን የምንገኘው የነቢያት ፆም አንዱ ነው፡፡ ይህ ፆም ነቢያት የጌታን መወለድ በታላቅ ፍቅርና በጉጉት ሲጠባበቁ የፆሙት ፆም ነው፡፡ ሲጠበቅ የነበረውም የዓለም መድኃኒት የሆነው መሲህ ጊዜው ሲደርስ ተወልዷል፡፡ ቤተ-ክርስቲያኒቷ ይህ ፆም እንዲ ፆም ያወጀችው ነቢያት  ፆመው በረከት አግኝተውበታና  አማኞችም ቢፆሙት በረከት ያገኙበታል የሚለውን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ነው፡፡ ቤተክርስቲያኒቷ ይህንን ፆም ከህዳር 14 እስከ  ታኅሳስ 29  ባሉት ቀናት  ውስጥ እንዲፆም በቀኖናዋ አውጃለች፡፡ በአራት ዓመት አንድ ጊዜ ግን በ28 ፆሙ ይፈታል፡፡ በእነዚህ ወራት ውስጥ ያሉት እሁዶች የራሳቸው የሆነ ስያሜ አላቸው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ከህዳር 27 እስከ ታኅሳስ 3 ቀናት ባለው ጊዜ ውስጥ የዋለ እሁድ መፃጉዕ በመባል ይታወቃል፡፡ የነገው እሁድ  በቀን አንድ ስለዋለ መፃጉዕ ይባላል ማለት ነው፡፡ በዚህ ዕለትም ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዕውርን ያበራበት፣ ድውን የፈወሰበት፣ ተስፋ የሌላቸውን ተስፋ የሰጠበት ዕለት እንደሆነ በቤተክርስቲያን እየታሰበ ይዘመራል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በቅዳሴግዜ የሚነበቡትን የመፅሐፍ ቅዱስ ክፍሎች  የሚያወጣው ግፃሚ/ማውጫ  ተብሎ  የሚጠራው መፅሐፍ በዕለቱ  እንዲሰበክ ያዘዘውን ምስባክና እንዲነበብ ያዘዘውን ወንጌል መሠረት አድርገን ሰፋ ባለ መልኩ በቅደም ተከተል በትንታኔ እንመለከታቸዋለን፡፡
መዝ 4÷2-3 “ደቂቀእጓለ እመሕያው እስከ ማዕዜኑ ታከብዱ ልበክሙ ለምንት ታፈቅሩ ከንቶ ወተሐሱ ሐሰተ አእምሩ ከመ ተሰብሐ እግዚአብሔር በፃድቁ”
ትርጉም “እናንተ የሰው ልጆች እስከ መቼ ድረስ  ልባችሁን ታከብዳላችሁ? ከንቱ ነገርን  ለምን ትወድዳላችሁ?ሐሰትንም ለምን ትሻላችሁ? እግዚአብሔር በፃድቁ እንደተገለጠ እወቁ”
መፃጉእ ማለት በሽተኛ፣በደዌ የተመታ፣ ሕሙም ማለት ነው፡፡መጽሐፍ ቅዱስን መሰረት አድርገን ስንነጋገር በሽታ የመጣው ከአዳምና ከሔዋን ውደቀት ጀምሮ ነው፡፡ ይህም በሽታ በኃጢአት ምክንያት ወደ ዓለም እንደገባ እንረዳለን፡፡ አዳም እና ሔዋን ከወደቁ በኋላ ወዲያውኑ ፍርሃትና ስቃይ ተሰማቸው ዘፍ 3÷10፡16፡17፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ መገለጫውን በፍርሃት እና በስቃይ የጀመረው በሽታየተለያየ ይዘት አለው፡፡ መንፈሳዊ ዕውርነት፣ የአዕምሮ በሽታ፣ ልዩ ልዩ የሰውነት በሽታ፣ ልዩ ልዩ የውስጥ ደዌ በሽታ፣ ወዘተ….ብለን ልንዘረዝረው እንችላለን፡፡ በሌላ መልኩ ለእግዚአብሔር አለመታዘዝ ተወዳዳሪ የሌለው ትልቁ የዓላማችን በሽታ ነው፡፡ ከላይ ያነሳነው መዝ 4÷2-3 ላይ የሚገኘው የእግዚአብሔር  ቃል ይህንን እውነት ያረጋግጥልና፡፡ በዚያን ዘመን የነበሩት  የሰው ልጆች ልባቸውን ምን ያህል እንዳከበዱ፣ ከንቱ ነገርን እንደወደዱና ሐሰትንም የሚሹ  መሆናቸውን ይገልፃል፡፡ የሰው ልጅ ልቡን ካከበደ አስከፊ በሆነው የአለመታዘዝ በሽታ ውስጥ እተሰቃየ ነው፡፡ከእግዚአብሔርእየራቀ እና ሕይወትን እያጣ ይሄዳል፡፡
ልቡን ያከበደ ሰው ሀሰቡ  ደንድኗል ማለት ነው፡፡ ልባቸውን የሚያከብዱ በልባቸው ለእግዚአብሔር ስፍራ የላቸውም፡፡ ይህ ማለት በሃሳባቸው ውስጥ እግዚአብሔርን አያነግሱም፡፡ ስለዚህ ይህ ደግሞ አደገኛ አስከፊ በሽታ ቢባል ያንሰዋል እንጂ አይበዛበትም፡፡ እግዚአብሔርን ያላነገሱ ልቦች ውጤት ደግሞ ከንቱ  የሆነውን ነገር ነው በልባቸው የሚያነግሱት፡፡ በከንቱ ተሞልቶ መመላለስ  የሐሰት መንገድ ነው፡፡ ለዚህ ነው ቃሉ “እናንተ የሰው ልጆች እስከመቼ ድረስ ልባችሁን ታከብዳላችሁ? ከንቱ ነገርን ለምን ትወድዳላችሁ? ሐሰትንም ለምን ትሻላችሁ?እግዚአብሔር በፃድቁ እንደተገለጠ እወቁ” የሚለን፡፡ ዛሬም ቢሆን ብዙዎች ለእግዚአብሔር ቃል ጊዜ የለንም፣ እግዚአብሔርን አንሰማም የሚሉ ነገር ግን በልባቸው ኃላፊና ጠፊ የሆነው የዚህ ዓለም ጣጣ የነገሰባቸው፣በልባቸው ለእግዚአብሔር  ስፍራ የሌላቸው፣ ሁሌም ጊዚያዊ ለሆነው ነገር ብቻ የሚሯሯጡ አሉ፡፡ ይህ ግን ውጤቱ ዜሮ ነው፡፡ የሚሻለውና አማራጭ የሌለው ጉዳይ ወደ እግዚአብሔር መመለስ ነው፡፡ እግዚአብሔር የጨለመን ልቦና በራሱ ቃል ማብራት ይችልበታል፡፡ ልብ የእግዚአብሔርን ቃል ለመቀበል በመንፈስ ቅዱስ በኩል በፀጋው መረሰረስ አለበት፡፡ ንፁህ ልብ በእግዚአብሔር ዘንድ እጅግ ተወዳጅ ነው፡፡ ማቴ 5÷8 “ልበ ንፁሖች በፁዓን ናቸው እግዚአብሔርን ያዩታልና”  ነው የተባለው፡፡ እግዚአብሔርን ለማየት የሀብት ብዛት፣ ገንዘብ፣ ዝና፣ ስልጣን፣ የትምህርት ደረጃ፣ የጤና ጉዳይ፣ የዕድሜ ጉዳይ መስፈርት ሆኖ አልተቀመጠም፡፡ መስፈርቱ ንፅህ ልብን መያዝ ነው፡፡
 በዕለቱ የሚነበበው ወንጌል በዮሐንስ ወንጌል ምዕ 9÷1 እስከ ፍፃሜ ያለው የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቃል ሲሆን ይህ ምዕራፍ 41 ቁጥሮች ሲኖሩት አንድ ዕውር ሆኖ ስለተወለደ ሰው፣  ይህ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ከዕውርን እንደተላቀቀ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን ሰው ለምን በሰንበት ፈወሰው ብለው ፈረሳውያን ፀብ ማንሳታቸው፣ የፈረሳውያንን መንፈሳዊ ዕውርነት፣ የተፈወሰው ሰው በፈረሳውያን ከምኩራብ መባረር እና የተባረረውን ሰው ክርስቶስ በውጭ ሆኖ መቀበሉ የምዕራፍ ዋና ዋና ሃሳቦች ናቸው፡፡ ጌታችን መድኃኒታእን ኢየሱስ ክርስቶስ ክርስቶስ ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደበት ትልቁ ዓላማ የሰው ልጆችን ለማዳንና የዘላለም ሕይወትን ለመሰጠት ነው፡፡ 1 ዮሐ 4÷14 “እኛም አይተናል አባትም ልጁን የዓለም መድኃኒት ሊሆን እንደላከው እንመሰክራለን” ይላል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የሥጋም የነፍስም መድኃኒት ነው፡፡ ደግሞም ለዓለም ሁሉ የሚበቃ መድኃኒት ነው፡፡ ኢየሱስ ማለት አዳኝ፣ መድኃኒት ማለት ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማንኛውንም ዐይነት በሽታና ደዌ መፈወስ ይችላል፡፡ በዚህ ባነሳነው ምዕራፍ ላይ ከልደቱ ጀምሮ ዕውር ሆኖ የተወለደውን ሰው ክርስቶስ እንደፈወሰው እናነባለን፡፡ በእግርጥ ደቀ መዛሙርቱ እንደጠየቁትና ኢየሱስ ክርስቶስም እንደመለሰው ይህ  ሰው ዕውር ሆኖ  የተወለደው የእግዚአብሔር ስራ በእርሱ እንዲገለጥ ነው እንጂ እርሱ ወይም ወላጆቹ ኃጢአት ሰርተው እንዳልሆነ ገልጿል፡፡
ጠቅለል ባለ መልኩ መፃጉእ በሚለው ርእስ ካነሳነው ትምህርት የሚከተሉትን እውነቶች እንረዳለን÷
1∙ ኢየሱስ ክርስቶስ  የዓለም መድኃኒት መሆኑን÷ ቀደም ሲል እንዳነሳነው ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም የመጣበት ዋነኛ ዓላማ በኃጢአት የወደቀውን የሰው ልጅ በጽድቅ ለማንሳት፣ የስጋንና የነፍስንም ደዌ ሊፈውስ ነው። ፈዋሽ መሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ተገልጿል። “መዳንም በሌላ በማንም የለም እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና” የሐዋ 4:12። ይህ የሚያስረዳን ኢየሱስ ክርስቶስ ለማንኛው በሽታና ደዌ ፍቱን መድኃኒት መሆኑን ነው። የሰማርያ ሰዎችም “… እርሱም በእውነት ክርስቶስ የዓለም መድኃኒት እንደሆነ እናውቃለን …” በማለት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
2 ∙ለመንፈሳዊ ዕውርነት መፍትሄው ክርስቶስ እንደሆነ÷ ኢየሱስ ክርስቶስ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ”(ዮሐ 8:12) ብሏል። ያኔ አዳምና ሔዋንን በገነት ውስጥ ያሳወረ ሰይጣን ዛሬም ቢሆን ብዙዎችን ለማሳወር እንደተራበ አንበሳ አያገሳ ይዞራል  ። ለዘህ ደግሞ ትልቁ መፍትሄ መንፈሳዊ ጨለማን ወደ ሚያርቀው ወደ ክርስቶስ መጠጋት ነው። ወደ እርሱ መጠጋት ማለት በእርሱ መኖርና ከመንፈሳዊ ዕውርነት  መላቀቅ ማለት ነው።
3∙ ላዳነንና ብርሃን ለሰጠን አምላካችን መስካሪዎች መሆን እንዳለብን÷ በጨለማ ዓለም ውስጥ ስለ ብርሃን መመስከር ዋጋ የሚያስከፍል ነገር ቢሆንም ልባችንን ከጨለማና ከዕውርነት ስላወጣው ብርሃናችን የመመስከር መንፈሳዊ ግዴታ አለብን። ብርሃናችን እርሱ ክርስቶስ ነው። በአምላካችን ቸርነትና ምህረት ደኅንነትንና ብርሃንን ካገኘን ለሌሎችም በኃጢአት ሕይወት ውስጥ ላሉት ስለ ብርሃናችን ክርስቶስ እየነገርናቸው ከጨለማ እንዲወጡ ማድረግ አለብን። ውድ አንባብያን ሆይ በመልካም መንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ ዘመናችንን እንድናሳልፍ እግዚአብሔር ይርዳን አሜን ።
                       
                                           ወስብሐት ለእግዚአብሔር 

 

አድራሻ

አዲስ አበባ ፤ ኢትዮጵያ

ኢ-ሜይል: aadioces@gmail.com

ድረ ገጹ ውስጥ ይፈልጉ

ሀሳበ ባሕር(የዘመን ቁጥር)

ባሕረ ሐሳብ የዘመን መቁጠሪያ

ግጻዌ