መንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም

የምዕራብና የደቡብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ገነተ ጽጌ ቅ/ጊዮርጊስ

የምዕራብና የደቡብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔዓለም

የምዕራብና የደቡብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

መንበረ ጸባዖት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል

የምዕራብና የደቡብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ርዕሰ አድባራት መንበረ ፀሐይ እንጦጦ ማርያም

የምዕራብና የደቡብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ምስካየ ኅዙናን መድኃኔኃለም ገዳም

የምዕራብና የደቡብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም

የምዕራብና የደቡብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ደብረ ጽጌ ቅድስ ኡራኤል

የምዕራብና የደቡብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

መንበረ መንግሥት ቅ/ገብርኤል ገዳም

የምዕራብና የደቡብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ደብረ ኃይል ራጉኤል

የምዕራብና የደቡብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

http://www.addisababa.eotc.org.et/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/590538kidste_mariam.jpg http://www.addisababa.eotc.org.et/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/895720giorgis.jpg http://www.addisababa.eotc.org.et/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/903816bole_medhaniealem.jpg http://www.addisababa.eotc.org.et/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/683566trinity.jpg http://www.addisababa.eotc.org.et/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/821897entoto_mariam.jpg http://www.addisababa.eotc.org.et/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/310283meskaye_1.jpg http://www.addisababa.eotc.org.et/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/904160BEATA_MARIAM.jpg http://www.addisababa.eotc.org.et/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/578084urael.jpg http://www.addisababa.eotc.org.et/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/812647gebrie_gedam.jpg http://www.addisababa.eotc.org.et/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/681179raguel.jpg
መልካም ባልንጀራ

ምስጢር የሚወያዩትን አብሮ የሚሠሩትንና ጧት ማታ የሚገናኙትን እንዲሁም አብሮ አደግ የሆነውን ሰው ባልንጀራዬ ነው ብሎ መናገር የተለመደ ነው፡፡ ዛሬ ለኔ ነገ ላንተ እየተባባሉ አብረው ከሚውሉት፣ ከሚያመሹት ጓደኞቻቸው ሌላ ባልንጀራ ያለ የማይመስላቸውም ብዙዎች ናቸው፡፡ በመሠረቱ አብሮ መብላትና መጠጣት ወይም በአንድ ላይ ተምሮ ማደግና አብሮ መኖር ይልቁንም ትንሽ ትልቁን ክፉና ደጉን ምስጢር መካፈል ባልንጀራ ሊያሰኝ ቢችልም ይህ ብቻ ራሱ የፍቅር መመዘኛና መለኪያ ይሆናል ማለት ዘበት ነው፡፡ ምክንያቱም በዚህ ሁኔታ የተመሠረተው ፍቅር አብዛኛውን ጊዜ በጥቅም ላይ የተመሠረተ ስለሚሆን ሰብአዊ ርኅራኄና ከልብ የመነጨ መንፈሳዊ ስሜት የተዋሐደው ሊሆን አይችልምና ነው፡፡
አንዳንድ ሰዎች ‹‹ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ፡ በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር፡ የባልንጀራህን ሚስት ቤትና ንብረት በአጠቃላይ የባልንጀራህን ገንዘብ ሁሉ ማንኛውንም አትመኝ›› የሚለውን ሕግ ከመጽሐፍ ቅዱስ ሲያነቡላቸውና በባልንጀራቸው ላይ ክፉ ሥራ እንዳይሠሩ ትምህርት ሲሰጧቸው ባልንጀራዬን እንዴት እከዳለሁ? እንዴትስ ተንኮል እፈጽምበታለሁ? በማለት ራሳቸውን ለባልንጀራቸው ታማኝ በማስመሰል ሊናገሩና ሊከራከሩ ይችላሉ፡፡ በሌላ በኩል ግን የተፈጥሮ ጓደኛቸው የሆነውን ሰብአዊ ፍጡር ሲያሳዝኑትና ሲያስቀይሙት ይታያሉ፡፡ እንዲህ ያለውን ክፉ ተግባር በሰዎች ላይ መፈጸም ‹‹ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ›› የሚለውን መጣስ ነውና ይህ ኃጢአት ነው ሲሏቸው ደግሞ ባልንጀራዬ ማን ነው? የማላውቀው ሰውስ እንዴት ባልንጀራዬ ይሆናል በማለት ድርቅ ብለው ይከራከራሉ፤ የሚበላና የሚጠጣ የጽዋ ጓደኛ ከዚህም ሌላ በሀብትና በእውቀት ተመጣጣኝ ሆኖ ውለታ የሚውልና ብድር የሚመልስ ወይም በሥጋ ተዛምዶ የሚቀርብና የሀገር የወንዝ ልጅ የሆነ አፈር ፈጭቶ ውኃ ተጎንጭቶ አብሮ ያደገ ወይም በአንድ ትምህርት ቤት አብሮ የተማረ በሥራና በጉርብትና ምክንያት ወቅታዊ ፍቅር የመሠረተና ምስጢር የተጫወተ …ወዘተ ብቻ ነው ብለው ስለሚያስቡ ነው፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ግን ‹‹ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ›› ሲል የተናገረው ማንኛውም ሰው በተፈጥሮ የሚመሳሰለው ሰብአዊ ፍጡር ሁሉ ባልንጀራው መሆኑን አውቆ አንዱ የሌላውን መብት በመጠበቅ እርስ በርሱ ተከባብሮና ተፈቃቅሮ በሰላምና በደስታ እንዲኖር ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ከሰዎች መካከል እኔን አይመለከተኝም ሳይል አንዱ ሌላውን እንዲረዳው ነው፡፡ ይህም አባባል ባልንጀራ በወገን፣ በጾታ፣ በጎሳ፣ በዘርና በመሳሰለው ጠባብ አስተሳሰብ ሳይወሰን እያንዳንዱ ሰው ለሌላው ሰው ወገኑና ባልንጀራው እንዲሁም ከአንድ ፈጣሪና ከአንድ አባት የተገኘ የተፈጥሮ ወንድሙ መሆኑን የሚያስገነዝብ ነው፡፡
በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 10 ላይ እንደተጻፈው ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማስተማር ላይ ሳለ አንድ ሕግ አዋቂ ሊፈትነው አስቦ፡- መምህር ሆይ የዘለዓለም ሕይወትን እወርስ ዘንድ ምን ላድርግ? በማለት በጠየቀው ጊዜ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሕግ የተጻፈው ምንድን ነው? አለው፡፡ ሕግ አዋቂውም መልሶ፡- ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህ በፍጹም ኃይልህ በፍጹም ሀሳብህ ውደድ ባልንጀራህንም እንደራስህ ውደድ ሲል መለሰ፡፡ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስም እውነት መልሰሀል ይህንን ብታደርግ በሕይወት ትኖራለህ ሲል ነገረው፡፡ ነገር ግን ሕግ አዋቂው ራሱን ከፍ አድርጎ በመመልከት ባልንጀራዬ ማን ነው? ሲል እንደገና ጠይቋል በዚህ ጊዜ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የደጉን ሳምራዊ ታሪክ ከተረከ በኋላ ‹‹አንተም እንደዚሁ አድርግ›› በማለት ለሰዎች ሁሉ መልካም መሥራትና እርስ በእርስ መዋደድ እንደሚገባ አስረድቶታል፡፡
እንግዲህ ባልንጀራ የሚባለው ባገኙ ጊዜ ብቻ አብሮ በልቶ ጠጥቶ በችግር ጊዜ ወደኋላ የሚሸሽ ሰው ሳይሆን ‹‹ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ›› በሚለው አምላካዊ ትእዛዝ መሠረት የችግረኞችንና ጉዳተኞችን ችግር እንደራሱ ችግር በመቁጠር ውለታና ብድር ሳይሻ ሁሉንም በእኩልነት ተመልክቶ በጤናም ሆነ በሀብት ወይም በእርጅና ምክንያት የተቸገሩትን ሁሉ በአቅሙ መጠን የሚቻለውን የሚረዳ ነው፡፡ ከዚህም ሳምራዊ ሰው የምንማረው ይህንኑ ነው፡፡
እኛም እንደደጉ ሳምራዊ ሰው በመዋዕለ ዘመናችን ሁሉ ለሰዎች መልካም አድርገን በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት እንዲሁም በቅዱሳን አማላጅነት መንግሥተ ሰማያትን እንድንወርስ ልዑል እግዚአብሔር ወሰን በሌለው ቸርነቱ ይርዳን፡፡ ወስብሐት ለእግዚአብሔር::
(ላዕከ ወንጌል በእደ ማርያም ይትባረክ (ቀሲስ) የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የትምህርት ሥርጭት ኃላፊ)

 
የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በቅጥረ ግቢው መካነ መቃብር ዙሪያ በሶሻል ሚዲያ ላይ ለተሰራጨው መሠረተ ቢስ ዘገባ ማብራሪያ ሰጠ

pp002

በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እና በበዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን መካነ መቃብራት የሚገኙ ዐፅሞች እንዲፈልሱ የተወሰነው፣ በቦታው ሕንፃ ለመሥራት ተፈልጎ ሳይሆን፤ የመቃብር ቦታው በመሙላቱና በመጨናነቁ እንደሆነ የካቴድራሉ አስተዳደር አስታወቀ፡፡
ሊቀ ሥልጣናት አባ ገብረ ሥላሴ በላይ፣ የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እና የበዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ፣ ስለ ጉዳዩ ከሰንደቅ ጋዜጣ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፥ መካነ መቃብራቱን ከማልማት፣ ከማስዋብና ከመከባከብ ውጭ ሕንፃ የመገንባት ዕቅድ አስተዳደሩ ፈጽሞ እንደሌለው አረጋግጠዋል፡፡ 
ካቴድራሉ በቅጥር ግቢው ከሚገኙ መካነ መቃብራት ውስጥ፣ በበዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን ደቡባዊ ክፍልና በካቴድራሉ መካከል የሚገኘውን የመካነ መቃብር ሥፍራ ለማልማት እንዲቻል፥ በጋዜጦች፣ በራዲዮና በቴሌቭዥን ቤተሰቦች ተገኝተው ዐፅሞችን እንዲያነሡ ጥሪ መተላለፉን ሊቀ ሥልጣናቱ ጠቅሰው፤ በጥሪው መሠረት የተገኙ ቤተሰቦች ባደረጉት ትብብርና ስምምነት መሠረት ዐፅሞቹ በክብር እንዲነሡ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
የማፍለስ ሒደቱም በሁለት ዓይነት መልኩ እንደተከናወነ፣ ሊቀ ሥልጣናት አባ ገብረ ሥላሴ ያስረዳሉ፡፡ ይኸውም፣ በመካነ መቃብሩ ላይ የሚገኙ ሐውልቶች ብቻ ተነሥተው አዕፅምቱ ሳይነሡ፣ ስማቸውና ታሪካቸው በግድግዳ ላይ እንዲጻፍ መደረጉን፤ በሌላ በኩል ደግሞ፣ ሙሉ በሙሉ ከመካነ መቃብራቱ ተነሥተው በተዘጋጀላቸው ሥፍራ እንዲያርፉ የተደረጉ አዕፅምት መኖራቸውን አስረድተዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ እንዲነሡ ከተደረጉት ከ290 ያላነሱ አፅሞች መካከል፦ የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ፣ የመልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ እና የፕሮፌሰር ዐሥራት ወልደየስ እንደሚገኙበት ዘርዝረዋል፡፡
የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ ቤተሰቦች በወቅቱ ባለመምጣታቸው፣ ዐፅማቸው ከመካነ መቃብሩ ተነሥቶ በክብር በተዘጋጀለት የካቴድራሉ ቦታ ያረፈው የዛሬ ስምንት ዓመት መሆኑን ያዘከሩት ሊቀ ሥልጣናቱ፥ በቅርቡ ግን፣ ቤተሰቦቻቸው መጥተው ወደ ትውልድ ሥፍራቸው ወስደው ማሳረፍ እንደሚፈልጉ በመግለጻቸው፣ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን መሠረት ተገቢው ጸሎት ተደርሶ በክብር እንደ ተሸኘ አስረድተዋል፡፡ ይህን አስመልክቶ በተለይ በማኅበራዊ ድረ ገጾች የተዛቡና እውነት ያልሆኑ መረጃዎች መሰራጨታቸው ካቴድራሉን እንዳሳዘነም ጠቁመዋል፡፡የመልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬን ዐፅም ወደ ካቴድራሉ መካነ መቃብር ለማፍለስ፣ ወንድማቸው መጥተው የነበረ ቢሆንም፣ በዐቅም ማነስ ምክንያት ወደ ካቴድራሉ ማሳረፊያ ማንሣት እንደማይችሉ ተናግረዋል፡፡ በዚህም ምክንያት፣ “የካቴድራሉ አስተዳደር ሐውልቱን በማንሣት ዐፅማቸው ባለበት እንዲቆይና ስምና ታሪካቸው በግድግዳ ላይ እንዲጻፍ ወስኖ ነበር፤” ብለዋል ሊቀ ሥልጣናቱ፡፡ ሆኖም በአሁኑ ወቅት፣ የልጃቸው ባለቤት የሆኑ ግለሰብ ቀርበው በማመልከታቸው፣ ካቴድራሉ፥ የመልአከ ብርሃን አድማሱን ዐፅም ሌላ ቦታ ሰጥቶ ለማፍለስና ለማሳረፍ እየተዘጋጀ እንዳለ አስተዳዳሪው አስታውቀዋል፡፡
የበዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን በያዛቸው ሐውልት/ቀብር/ ቤት እና የመቃብር አጥር ብዛት ቅጽረ ግቢው ለማስቀደሻ እየጠበበ መሆኑን የሚጠቅሰው የካቴድራሉ “የቀብር የሐውልት ማሥነሻ ቅጽ”፣ ዐፅሙ ባለበት እንዲሆንና ቦታው ተስተካክሎ ለምእመናን ማስቀደሻ – መጠለያ እንደሚሠራበት ያመለክታል፤ ለዚህም ተግባር የሟች ቤተሰብ ያለምንም ቅሬታ ተስማምቶ ለሥራው ተባባሪና የሚፈለገውን ድጋፍ ለማድረግም ፈቃደኛ እንደሆነ በፊርማው ማረጋገጡን ይገልጻል፡፡
የበዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን – በዐፄ ምኒሊክ ዘመነ መንግሥት፤ የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ደግሞ፣ በቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ መተከላቸውን፤ የቀብር አገልግሎቱ የተጀመረውም፦ ንጉሠ ነገሥቱ ከነቤተሰቦቻቸው የቀብር ቦታ ካዘጋጁና ለሀገራቸው የተዋደቁ ጀግኖች እንዲቀበሩበትና በሌላም ቦታ የተቀበሩት ዐፅማቸው እንዲያርፍበት ከፈቀዱ በኋላ መሆኑን ሊቀ ሥልጣናቱ ጨምረው አስታውሰዋል፡፡ የመቃብር ቦታው፣ ከ60 ዓመታት ላላነሰ ጊዜ እንዳገለገለም በካቴድራሉ የሚገኙ ሰነዶች ያረጋግጣሉ፡፡
ሊቀ ሥልጣናቱ አያይዘውም፥ ቤተሰቦች ከቀብር በኋላ የመቃብር ሥፍራዎችን የመጠበቅ፣ የመከባከብና የማስዋብ ሥራ እንደማይሠሩ ተችተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት፣ በተለይ ከ127 ዓመታት በላይ የዕድሜ ባለጸጋ የሆነው የባለወልድ ቤተ ክርስቲያን የመቃብር ስፍራ፣ ወደ ቆሻሻ መጣያነት ተቀይሮ መቆየቱ አሳዛኝ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ካቴድራሉ፥ ከመዲናዪቱ የቱሪስት መስሕቦች አንዱ እንደመሆኑ መጠን፣ የመካነ መቃብሩ አያያዝ የሀገር ገጽታንም የሚያበላሽ እንደነበር አስገንዝበዋል፡፡
ምንጭ፡-ሰንደቅ ጋዜጣ፤  ረቡዕ፣ ሐምሌ ፭ ቀን 2009 ዓ.ም.

 
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለአምስት ተከታታይ ቀናት ሲሰጥ የነበረው ሥልጠና ባለ 14 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቀቀ

1018

ሙሉ ዝርዝሩን ከዚህ ቀጥሎ እንደሚከተለው ይቀርባል
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ዋና አዘጋጅነት እና በኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር ትብብር በሥሩ ለሚገኙ የሀገረ ስብከቱ የመምሪያ ኃላፊዎች የሁሉም ክፍለ ከተማ የክፍል ኃላፊዎች የአብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎችና ዋና ፀሐፊዎ የሙያ ማጠናከሪያ ሥልጠና ቃለ ጉባኤና የአቋም መግለጫ
የስልጠናው መሪ ክቡር መምህር ጎይቶም ያይኑ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ
የስልጠናው ቀን ከሰኔ 19-23 ቀን 2009 ዓ.ም
የስልጠናው ሰዓት ከጠዋቱ 2፡30 እስከ 11፡00 ሰዓት
የስልጠናው ዓላማ የሥራ ኃላፊዎች የተጣለባቸውን የቤተክርስቲያን አደራና የሕዝብ ኃላፊነት በበለጠ ብቃትና ቅንነት ሥራቸውን እንዲያከናው ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ ሲሆን የሥልጠናውን መርሐ ግብር ለመጀመር በፀሎት ተከፍቷል፡፡
በመቀጠል የዕለቱ መርሐ ግብር መሪ ሥልጠናውን ለመጀመር የእንኳን ደህና መጣችሁና የመግቢያ ንግግር እንዲያደርጉ ክቡር የሀገረ ስብከቱን ዋና ሥራ አስኪያጅ ጋብዘዋል፡፡
በዚህም መሠረት ክቡር የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መምህር ጎይቶም ያይኑ ጥሪያችንን አክብራችሁ ለለውጥ በመነሳሳት ስለተገኛችሁ በሀገረ ስብከቱ ስም ልባዊ ምስጋናዬን እያቀረብኩ በአለፉት ጊዜያት በየአብያተ ክርስቲያናቱ በተለያየ የሥራ መስክ ያሉ በሂሳብና ገንዘብ ነክ ሥራ ላይ ለሚገኙ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ስልጠና የተሰጠ ሲሆን አሁን ደግሞ አስተዳዳሪዎችና ዋና ፀሐፊዎች የተዘጋጀውን ስልጠና ለዚሁ ስልጠና ከተዘጋጁ እውቅ ባለሙያዎች የሚሰጠውን ወቅታዊ የአሰራር ዘዴ በመቅሰም ከወቅቱ አሰራር ጋር እራሳችንን በማገናኘት በየምንመራቸው አብያተ ክርስቲያናትም ሰላማዊ፣ ግልጽና ተጠያቂነትን ያማከለ አስተዳደር ለመፍጠር ሲሆን ሁሉም በየድርሻው ብቃትና አቅም ቢኖርም ከወቅታዊ አሰራር ጋር አገናኝቶ/አቀናጅቶ/ ሥራን በተቀላጠፈና ታአማኒነት ያለው ለማድረግ ስልጠና አስፈላጊ በመሆኑ ዘመኑንም እየተመለከትን አሰራራችንን ማስተካከልና በምእመናን ዘንድ ተቀባይነትን እንዲያገኝ ለማድረግ ስልጠናው አስፈላጊ መሆኑን ተረድተን በንቃት እንድንሳተፍ እያሳስበኩ መልካም የስልጠና ሳምንት እንዲሆን በመመኘት ስልጠናውን በይፋ ከፍተዋል፡፡

09240


ለስልጠናው የተዘጋጁ ርዕሶች
1.ስኬታማ የሥራ ፈጠራ ጥበብ በዶ/ር ወሮታው በዛብህ
2.የፋይናንስ አመራር ጥበብና የሂሳብ መመሪያ አተገባበር በመብራቱ ባይህ
3.ሕግና ሕገ ቤተክርስቲያን መ/ር ቢተው ካሳው
4.መሪነትና ሥራ አመራር በአቶ አለማየሁ ተክሉ
5.ስለ መጽሐፍ ቅዱስ አመሰራረትና አሁን ያለበት ደረጃ በቀሲስ ይልማ ጌታሁን
6.ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያንና ኅብረተሰባዊ ለውጥ …በቀሲስ አሉላ ለማ
7.ስብከተ ወንጌል ከዘመነ ሐዋርያት እስከ ዛሬ በመጋቤ ብሉይ አእመረ አሸብር
በሚሉ መሠረታዊ ነጥቦች ስልጠናው የተሰጠ ሲሆን በዚሁ መሠረት ስኬታማ የሥራ ፈጠራ ጥበብ በሚለው ርዕስ ላይ ሁለት ዋና ዋና የሀብትና የስኬታማ ህይወት ምንጮች በመጥቀስ

እነሱም
1.አእምሮ
2.ጊዜ መሆናቸውና በነዚህ ላይ ሰፊ ውይይትና የቤተክርስቲያን መሪዎች ሊሰሩበትና ሊተገብሩት የሚገባ እንዳለ በጥያቄ መልክ አስቀምጠዋል፡፡
እነሱም
•የአእምሮ ድርቅ ከተፈጥሮ ድርቅ በላይ ሀገራችንን የጎዳ መሆኑ ለዚህም ማሳያ አብዛኛው ሕብረተሰብ መስራት ሲችል በልማናና በስደት እየተሰቃየ መሆኑ፤
•በተለያዩ ሱስ ቤቶች ወጣቱ በመቀመጥ ለሱስ ተገዥ መሆኑ፤
•ቤተክርስቲያን ሰፊ መሬት ይዛ በአንፃሩ ደግሞ ሰፊ ለማኞች በስሯ ያሉ መሆኑ፤
•በእቅድ ያልተያዘ ጊዜ ጥፋትን የሚያስከትል መሆኑ፤
•ሐብት ማለት ጊዜ መሆኑን አለመረዳት፤
•ጊዜን በእቅድ አለመምራት፤
•ጊዜንና አእምሮን በአግባቡ አለመጠቀም፤
ከዚህ በላይ የቀረቡት ዋና ዋና ነጥቦች ሲሆኑ በዚህ ላይ የቤተክርስቲያን አባቶች ሚናችን ምንድን ነው ሰርተናል ወይ? እራሳችሁን ጠይቁ ካሉ በኋላ አእምሮ ከዳነ ሁሉ ነገራችን ይድናል ለዚህ ደግሞ እናንተ ከፈጣሪ በተሰጣችሁ ፀጋ አማኙን ህብረተሰብ ወደ እግዚአብሔር መንግስት እንዲቀርብ አእምሮውንና ጊዜውን በበጎ ነገር ላይ እንዲያኖር የመምከር የመገሰጽ ብሎም የመገዘት ሥልጣን የናንተ ስለሆነ በዚህ ላይ ከፍተኛ ሥራ በመስራት ነፍስ የማዳን ሥራ መስራት እንደሚጠበቅብን በሰፊው በስልጠና መልስ ሰጥተዋል፡፡ ይህንን ካደረግን ስኬታማ ሰዎች በመባል እንታወቃለን ስኬት ሲኖር ደግሞ የሥራ ፈጠራ ችሎታችን የዳበረ ይሆናል በማለት ሰፊ ገለጻ ተደርጓል፡፡ በመቀጠል የፋይናንስ አመራር ጥበብና የሂሳብ መመሪያ አተገባበር በሚለው ላይ የገንዘብ ነክ የእውቀት መለኪያዎች ዋና ዋና ነጥቦች
•የበለጠ ገንዘብ ማግኘት
•ገንዘቡን መከላከልና መጠበቅ
•ገንዘባችንን መበጀት
•ለገንዘብ ዋጋ መስጠት
•ገንዘብ ነክ መረጃዎችን ማሻሻል
•ሞዴሊንግ ወይም ቤንች ማርክ ማስቀመጥ
•ውጤታማ የፋይናንስ እና የቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡በነዚህ ነጥቦች ላይ በሰፊው በመወያየትና ስልጠናውን በማዳበር በቤተክርስቲያናችን የገንዘብና የሀብት ብክነት እንዳይፈጠር እኛ ኃላፊዎች በሕጋዊ መልኩ የሚዘረጉ የወጭ ስልቶችን ከበላይ መስሪያ ቤት የሚተላለፉ ሕጎችና ደንቦችን ተከትለን ከሰራን ቤተክርስቲያናችን ከምንም በላይ የለውጥ ሃዋርያነቷን በመያዝ ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች በማከናወን ለተቋሟም ሆነ ብሎም ለሀገር ከፍተኛ ውጤት እንደምናሳይ በማስገንዘብ አሰራራችን ዘመኑን የዋጀ መሠረታዊ የሒሳብ አያያዝ መርሆዎችን በመዘርጋት በጥበብ በመመራት ከዳር ማድረስ እንደሚገባንና የቤተክርስቲያችንን ህልውና በመጠበቅና በማስጠበቅ መስራት የእኛ የሥራ ኃላፊዎች ድርሻ መሆኑን በማስረዳት ያጠቃለሉ ሲሆን በይቀጥላል ሕግና ሕገ ቤተክርስቲያን በሚል ርዕስ ቤተክርስቲያችን ሕግን የማስፈጸም ሂደቱ ምን ይመስላል በማለት የሕግን ትንታኔ ትርጉም እንደሚከተለው አስቀምጠዋል፡፡
•ሕግ ማለት በሰውና ባለው ነባራዊ ሁኔታ የሚገዛ መመሪያ ማለት ነው
•ሕግ ማለት ገዥና አስተማሪ ማለት ነው ሕግን የሚያወጣው ማነው እንደ ቤተክርስቲያናችን ሕግ የሕግ ባለቤት መስራች /አውጭው/ ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን መገንዘብ ነው ለዚህም ማስረጃ
•መጽሐፍ ቅዱስ
•ፍትሃ ነገስት
•ፍትህ መንፈሳዊ የሚጠቀሱ ሲሆን ቀደም ሲል የነበሩም ሆኑ አሁን ላለው ሕገ መንግስት ቤተክርስቲያናችን ለሀገር ያበረከተችው አስተዋጽኦ ቀላል እንዳልሆነ የሚያስረዳና የሚያሳይ ነው፡፡
ሕግ በሁለት ይከፈላል
1.ማህበራዊ ህግ ይባላል /የመንግስት ሕግ/
2.የወል ሕግ ይባላል /ሃይማኖታዊ ዶክትሪን ያለው/
መሆኑን በማስረዳት እንደቤተክርስቲያችን ደግሞ ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ የቀደሙ አባቶቻችን ቃለ አዋዲ በሚል የቤተክርስቲያን መተዳደሪያ ደንብ በማውጣት እንሆ ለዛሬ የቤተክርስቲያናችን እድገት መሠረት ሆኖ እየተሰራበት እንደሚገኝ በሰፊው አስረድተዋል፡፡ በማያያዝም መንግስት ከሃይማኖት ተቋም ውስጥ ጣልቃ አለመግባት በአስተዳደር ሲሆን በሰላምና በልማት ዙሪያ ለህብረተሰቡ የሚጠቅሙ ነገሮችን ለማስከበር በጋራ ይሰራል፡፡
ስለሆነም ቤተክርስቲያናችን የራሷ ሕግ የሆነውን ቃለ ዓዋዲ መሠረት ያደረገ የልማት አውታሮችን በመዘርጋት ሃብትና ንብረቷን በአግባቡ በጋራ በመጠቀም ቅድስት ቤተክርስቲያናችንን እንድንጠብቅና እንድናስጠብቅ እዚህ የተገኘን መሪዎች ኃላፊነት ነው በሚል አጠቃለዋል፡፡ በመቀጠል መሪነትና ሥራ አመራርን በተመለከተ ሲሆን በመሪና ሥራ አመራር መካከል ያለውን አንድትና ልዩነት በሚል ርዕስ እያንዳንዱን ለመመልከት ተሞክሯል፡፡ በዚሁ መሠረት
መሪነት ማለት
•ሠርቶ ማሰራት
•ማድመጥ ክህሎትንና አርኪ አንደበት ባለቤት ሆኖ እራሱን አርአያ አድርጎ መስራት
•አዳዲስ አሰራሮችን በመፍጠር ውጤት ማሳየት
•የሰው ኃይልን ለውጤት ማብቃት
•ለጋራ ግብ መቆም
•ራዕይ ያለው መሆን
•ወሳኝ መሆን
•እራስን የማነቃቃት ክህሎትን ማዳበር ከተጠቀሱት ነጥቦች መካከል ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ
ሥራ አመራር ማለት በሰዎች አማካኝነት ተፈላጊ የሆነ ሥራ የመስራት ጥበብ ማለት ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ በሥራ አመራር ላይ የተለያዩ የለውጥ አመራር እንዳለ የተረዳን ሲሆን በዋናነት
•የለውጥ ምክንያቶች
•የለውጥ ግፊቶች
•ለውጥ የሚወደድባቸው
•ለውጥ የሚጠላባቸው
•በለውጥ ሂደት የሥራ አመራሩ ሚና
•ለለውጥ ምን መርህ ይኑር
•የለውጥ ሥራ አመራር መርሆች
•አለመግባባት ማስወገጃና ችግር ሲሆን እንዴት እንደሚፈታ
•የስነስርዓት መጉደል ምክንያቶች
•የተግባቦት ክፍተት
•የዲስፕሊን አጠባበቅ መርሆች
•የዲስፕሊን አይነቶች በሚሉ ርዕሶች ላይ ሰፊ ገለጻና ጉባኤውን ያሳተፈ ውይይት በቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ ጉባኤው ከፍተኛ ጥቅም አግኝተናል፡፡ አሁን በአለነው ደረጃ ልክ ወቅቱን የዋጀ ትምህርት አግኝተናል በማለት ወደፊት በዚህ ርዕስ ተጨማሪ ስልጠና እንደምናገኝ በመመኘት ለአሰልጣኙ ከፍተኛ የሞራል ድጋፍ በመስጠት አመስግኗል፡፡
በመቀጠል የመጽሐፍ ቅዱስ ማህበር ጠቅላይ ፀሐፊ በአቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር አመሠራረትና አሁን ያለበት ደረጃ በማጣቀስ ሰፊ ገለጻ የተደረገ ሲሆን በዚህ የምንገኝ የቤተክርስቲያን የሥራ ኃላፊዎች ይህ ማህበር ተጠናክሮ እንዲቀጥል በአላችሁ ኃላፊነት ምዕመናን የማህበሩ አባል እንዲሆኑ በየቤተክርስቲያችሁ ቅስቀሳ እንድታደርጉ በማለት ትምህርታዊ ሰሚናር ከማብራሪያ ጋር በሰፊው ተሰጥቷል፡፡ ቀጣይ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን እና ኅብረተሰባዊ ለውጥ በሚል በዋና ዋና ነጥቦች
•የቤተክርስቲያን ባህርይ እና ኃላፊነት
•ቤተክርስቲያን በማህበራዊ አገልግሎት
•ኅብረተሰባዊ ለውጥ /ማህበራዊ ለውጥ/
•የኅብረተሰባዊ ለውጥ ባህርያት
•የኅብረተሰባዊ ለውጥ ምክንያቶች
•የቤተክርስቲያን ሚና በኅብረተሰባዊ ለውጥ
•አሉታዊ የኅብረተሰባዊ ለውጥ ማሳያዎች
ሀ/ ገንዘብ ተኮር
ለ/ ጎጠኝነት
ሐ/ ዝሙት ተዳዳሪነት
መ/ ሱሰኝነት
•ቤተክርስቲያን ልትወስዳቸው የሚገቡ የመፍትሄ ሃሳቦች
oማህበራዊ አገልግቶችን ማጠናከር
oየምክክር አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን ማቋቋም
oየሠለጠኑ ካህናትን ማፍራት /በሥልጠና ማብቃት/ በሚሉ ርእሶች ላይ ያተኮረ ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቦ ሰፊ ውይይት በማድረግ በአጠቃላይ ቤተክርስቲያ የተሰጣትን ተልእኮ በአለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር አገናዝበን መስራት እንደሚገባንና ሕብረተሰባችን ወደ አልተፈለገ የኃጢያት ምንጭ ወደሆነው ሥራ እንዳይሄድ የሄደውንም ባለብን ኃላፊነት ዘር፣ ፆታ ሳንለይ በትምህርተ ወንጌል በማስተማርና በመምከር መመለስ ያለብን መሆኑን በመረዳት ኃላፊነታችንን እንድንሠጥ የቀረበ ጽሑፍ በመሆኑ ጉባኤው ተቀብሎታል፡፡
ስብከተ ወንጌልን በተመለከተ
ስብከተ ወንጌል ከዘመነ ሐዋያት እስከ ዛሬ ድረስ በሚል ርዕስ መምህሩ ሲያብራሩ
•የወንጌል ስምምነት
•የስብከተ ወንጌል አስፈላጊነት
•በሁሉም ዘመናት ስብከተ ወንጌል
•ስብከተ ወንጌል በዘመነ ሊቃውንት
•ስብከተ ወንጌልና ዘመናዊነት
•ስብከተ ወንጌልና ድኅረ ዘመናዊነት
•በአሁኑ ወቅት በስብከተ ወንጌል ላይ ያንዣበቡ ፈተናዎች በሚለው ዋና ዋና ርዕሶች ሰፊ ትምህርት የተሰጠ ሲሆን በዚህ ወሳኝ ወቅት ቤተክርስቲያን ከስብከተ ወንጌል የበለጠ ጠቃሚ ነገር የለም ወንጌል መልካም አስተዳደርን ያጠናክራል ብልሹ አሠራርን ይቀንሳል የምዕመናን ብዛት ይጨምራል ያመኑትንም ያፀናል ወንጌል ሙስናን ያስቀራል ይህ ማለት በወንጌል ሙስና አይሠራም ማለት ሳይሆን ወንጌልን በትክክል የሚያምኑና የሚታዘዙ እነርሱ ሙስናን ይፀየፋሉ፡፡
የእግዚአብሔር ገንዘብ አለአግባብ አይባክንም እንኳንስ የእግዚአብሔር የሀገርም/የመንግስትም እንዲሁም የሌላ የማንኛውም ሰው ገንዘብ ቢሆን አይባክንም እውነተኞች ውሉደ ወንጌል ታማኝ ባርያዎች ናቸው፡፡ ዛሬ አግኝተው ለጥቂት ጊዜ መደሰት ሳይሆን  ዛሬ በጥቂቱ ነገር ታምነው ነገ ለብዙ መሾምን ከእግዚአብሔር ይጠብቃሉና በማለት በእያንዳንዱ ርዕስ ሰፊ ትምህርትና ስልጠና የተሰጠ ሲሆን በተሰጠው ስልጠና መሠረት ከሰልጣኞች ጥያቄና ማብራሪያ እንዲሁም አስተያየቶች በሰፊው ቀርቦ ውይይት ከተደረገ በኋላ በስልጠናው መሠረት ለተግባራዊነቱ ሁላችንም የበኩላችንን አስተዋጽኦ የምናደርግ መሆኑን አፅንኦት ተቀብለናል፡፡
ማጠቃለያ
እኛ የአድባራትና ገዳማት እንዲሁም ካቴድራል አስተዳዳሪዎችና ዋና ፀሐፊዎ ከሰኔ 19 -23 ቀን 2009 ዓ.ም በተለያዩ ርዕሶች የወሰድነው ስልጠና ወቅቱን የዋጀ አሁን በአለንበት ደረጃ በተማርነው /በሰለጠነው/ መሠረት ወደ ተግባር የምንገባ ሲሆን የሀገረ ስብከታችን ዋና ሥራ አስኪያጅ እኛን በአለን እውቀት ላይ ጊዜውንና ወቅቱን አመላካች የሆነ እውቀት እንድናገኝ ውድ ጊዜዎትን መስዋዕት በማድረግ እኛን በማክብር ከእኛ ጋር ቁጭ ብለው ስልጠናውን የመሩና የተከታተሉ እንዲሁም በየእለቱ ለሚቀርቡ የውይይት ሃሳቦች ላይ በሚሰጡት ማብራሪያና መልስ ጉባኤውን ያስደመመና ያስደነቀ በመሆኑ ይህ የሚያሳየው ቤተክርስቲያናችን በመልካም አስተዳደር በልማት የተሳለጠች እንድትሆን ለማድረግ በአለዎት ሰፊ ራዕይ በመሆኑ ከፍተኛ ምስጋናና አክብሮት የምንሰጥዎና በማንኛውም ሁኔታ ከጎንዎ መሆናችንን እያረጋገጥን ይህ የተጀመረ የለውጥ ሂደት ተጠናክሮ እንዲቀጥል እኛም ለተግባራዊነቱ የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናደርጋን በማለት በሰልጣኞቹ ሠፊ ማብራሪያ ውይይት ተደርጓል ለቀረቡ ጥያቄዎችም ከምሁራኑ መልስ ተሰጥቷል፡፡
በመጨረሻ ክቡር የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መምህር ጎይቶም ያይኑ የማጠቃለያ ንግግር ሲያደርጉ እናንተ ጠርተን በወሰድናቸው የሥልጠና ጊዜ ውስጥ የጎደለውን ለመሙላት በአለን ላይ አጠናክረን ቅድስት ቤተክርስቲያችንን ለማገለገል ስለሆነ እናንተም የሀገረ ስብቱን ጥሪ አክብራችሁ ለለውጥ በመነሳሳት ያለምንም ችግር ፀጥታ በተላበሰ መልኩ ስልጠናውን በመከታተላችሁ እኔም በሀገረ ስብከቱ ስም ምስጋናዬን እያቀረብኩ እንግዲህ ሁላችሁም በተሰጠው ስልጠና መሠረት ወደ ታች ወርዳችሁ ለምትመሯቸው ካህናትና ምዕመናን ተግባራዊ እንድታደርጉ የለውጥ ሐዋርያም እንድትሆኑ የሚያግዝ ትጥቅ የያዛችሁ መሆኑን በውይይቱ ወቅት የነበረው ተሳትፎ የሚያሳይ እና ከዚህም በፊትም ከፍተኛ ዕውቀት እንዳላችሁ የማውቅ ቢሆንም ማነቃቅያ ለመፍጠር የተደረገ ስልጠና በመሆኑ ይህንኑ ተረድታችሁ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ በልጅነት መንፈስ እያሳሰብኩ በተጨማሪ በአሁኑ ሰዓት የቤተክርስቲያናችንን አገልጋይ ካህናትና ልዩ ልዩ ሠራተኞች እየጎዳ ያለው በቃለ አዋዲው አንቀጽ 60 የተደነገገውን የጡረታ መመሪያ ባለመተግበራችን አባቶቻችን ሆኑ ወንድሞች እረፍተ ዘመን ገትቶአቸው ከዚህ አለም በሞት በሚለዩበት ጊዜ ቤተሰቦቻቸው በችግር በመውደቅ የሊቃውንት አባቶቻችን ልጆችና ቤተሰቦች የጎዳና ተዳዳሪ ሆነው ማየታችን በጣም የሚያሳዝን በመሆኑ በዚህ ላይ ሀገረ ስብከታችን ጥናት አድርጎ ወደ ተግባር ለመለወጥ በሂደት ላይ ስለሆነ የጡረታ መብታችሁን ማስከበር የሁሉም ሠራተኛ ኃላፊነትና ግዳጅ ሲሆን ለአፈፃፀሙ ደግሞ በዚህ የተገኛችሁ የጉባኤው ተሳታፊዎች በዋናነት የእናንተ ሥራ ስለሆነ በዚህ ጉዳይ ተግታችሁ እንድትሰሩ በማለት ሐሳባቸውን ከሰጡ በኋላ ከተወያዮች የተሰጠ ሃሳብ የጡረታ ገንዘብ አለመቀመጡ ቤተክርስቲያንን በእጅጉ የጎዳ ለመሆኑ እረጅም ዘመን ያገለገሉ አባቶች ቤተሰቦቻቸው ያለረዳት መቅረታቸው አንዱ ጉዳት ሲሆን ሁለተኛው እነሱን ለመርዳት ያለተፈላጊ የሥራ ሙያ በቤተክርሰትያን ላይ የሚከማቸው የሠራተኛ ብዛት በዋናነት ተዘግቧል፡፡ በመሆኑም በዚሁ ሥራ ላይ ለመተግበር በጋራ እንሰራለን በማለት ጉባኤው የሚከተለውን የአቋም መግለጫ በጋራ አውጥተናል፡፡
የአቋም መግለጫ
1.ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ያላትን ሀብትና የምዕመናንን ዕውቀት ተጠቅማ ለአማኞቿ የተሟላ አገልግሎት በመስጠት ለሥራ አጥ ወገኖችም የሥራን ጥቅምና የሕይወትን ስኬት ከማስተማር ጎን ለጎን በየአብያተክርስቲያናቱ የልማት ተግባራትን ለማፋጠን ቃል እንገባለን፤
2.እኛ ኢትዮጵያውያን ከተፈጥሮ ችግር በላይ የአስተሳሰብ ደክመትና የጊዜ ብክነት እየጎዳን በመሆኑ ይህንን ክፉ የስንፍና በሽታ በትምህርተ ወንጌል በማከም የሕብረተሰቡ ዋና ክፍል የሆነው ወጣቱ ትውልድ ሥራ ፈጠራና ተነሳሽ በሥነ ምግባር የታነፀና ሀገሩን ወዳድ እንዲሆን የመሪነት ኃላፊነታችንን ለመወጣት ቃል እንገባለን፤
3.በየምንመራቸው አብያተ ክርስቲያናት ያለውን የገንዘብ እንቅስቃሴ በዘመናዊ አሠራር የተቃኘ ግልፅነትንና ተጠያቂነትን ያረጋገጠ አሠራር እንዲሰፍን የኃላፊነት ድርሻችንን ለመወጣት ቃል እንገባለን፤
4.ሰብዓዊ መብት የሰው ልጅ በሕገ ተፈጥሮ ከእግዚአብሔር የተጎናፀፈው ፀጋ በመሆኑ ለሠራተኞች ሕጋዊ አሠራርን በመከተል ሰብዓዊ መብታቸው ተከብሮ ለልማትና እድገት እንዲነሳሱ የኃላፊነታችንን ድርሻ ለመወጣት ቃል እንገባለን፤
5.በሥራ አመራር ባህርያት ወቅታዊ የሆነውን አሳታፊና ሳይንሳዊ ይዘት ያለውን መርህ በመከተል ፍትሐዊ የሆኑ አሠራሮቹን በመተግበር የቤተክርስያኒቱን አካላት ባሳተፈ መልኩ ሥራችንን ለማከናወንና ኃላፊነታችንን ለመወጣት ቃል እንገባለን፤
6.ቅድስት ቤተክርስቲያናችንን በራሷ ሕግ ፍትህ መንፈሳዊ መስጠቱን የምንደግፈውና የምንቀበለው ቢሆንም የፍትህ አካላት በሚሰጡት ውሳኔ ከማንኛውም አስተዳደራዊ ተፅዕኖ ነፃናቸው በሚለው መርህ መሠረት በብቁ ባለሙያዎች የፍትህ ሥራው እንዲከናወን እንጠይቃለን፤
7.ከመንግስታዊ ተቋማት የሚቀርቡ የግብርና የተለያዩ የክፍያ ጥያቄዎች በአፈፃፀም የተቸገርንባቸው በመሆኑ በሀገረ ስብከታችን ተገቢው ጥናት ቀርቦ ውሳኔ እንዲያገኝና ወጥ የሆነ የአሰራር መመሪያ እንዲደርሰን እንጠይቃለን እኛም ከሀገረ ስብከቱ ጎን ተሰልፈን ለውጤታማነቱ የበኩላችንን ድርሻ እንወጣለን፤
8.የሀገረ ስብከታችን ዋና ሥራ አስኪያጅ ይህንን ስልጠና በማዘጋጀት ወቅታዊ አሰራርን በመከተል ሰላማዊ አስተዳደር እንዲኖር ያደረጉትን ጥረት እያደነቅንና ልባዊ ምስጋናችንንም እያቀረብን በቀጣይም ይህ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንጠይቃለን፤
9.ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያናችን ከጥንት ጀምሮ የሕብረተሰቡን ችግር በመቅረፍ ታሪክ የመሰከረላት በመሆኑ ይህንን ለማስቀጠል የሚያስችሉ የምግባረ ሠናይ በጎ አድራጊ እና የምክክር አገልግሎት ክፍሎችን አጠናክረን እንደምናስቀጥል ቃል እንገባለን፤
10.ሀገረ ስብከታችን በአሁኑ ጊዜ ሰላማዊና ፍትሐዊ አስተዳደር ያለው በመሆኑ ሁከት ተወግዶ ፀጥታ የሰፈነበት ወቅት ስለሆነ ይህ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እየጠየቅን የሀገረ ስብከቱ ቀጥተኛ ተጠሪዎችም በስልጠናው ያለን አካላት በመሆኑ የሥራ ግንኙነቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እየጠየቅን እኛም ለስኬታማነቱ የበኩላችንን ድርሻ እንደምንወጣ ቃል እንገባለን፤
11. ቅድስት ቤተክርስቲያናችን የሕግና ሥርዓት ባለበት በመሆኗ አባቶቻችን ያቆዩት ቀኖና ቤተክርስቲያን ተጠብቆ እንዲቆይ ሁላችንም እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነን ድርሻችንን እንደምንወጣ ቃል እንገባለን፤
12.የስብከተ ወንጌል አገልግሎት የቅድስት ቤተክርስቲያናችን ተቀዳሚ አላማና ተግባር በመሆኑ ለአማኞቻችን ሕይወትን የሚሰጥ ወንጌል እንዲሰበክና ቤተክርስቲያናችንም ባመነችባቸው ሊቃውንት እንዲሰጥ የምናደርግና በቀጣይም ለተፈፃሚነቱ በተዋረድ ለሰባኪያነ ወንጌልና ለሌሎች አገልጋይ ሠራተኞች ስልጠናውን ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሀገረ ስብከቱን የስብከተ ወንጌል መምሪያ ተገቢውን ጥረት እንዲያደርግ እንጠይቃለን፤
13.ለቅድስት ቤተክርስቲያናችን ሁለንተናዊና መንፈሳዊ አገልግሎት መጠናከርና ተረካቢ አገልጋይ ለመፍጠር የአብነት ትምህርቶች ምንጭ በመሆናቸው ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚያስፈልገውን ድጋፍ ለማድረግ ቃል እንገባለን፤
14.በቅድስት ቤተክርስቲያናችን የምንገኝ አገልጋይ ካህናትና ሠራተኞች ከአገልግሎት የዕረፍት ዘመናችን በኋላ ለችግር እንዳንጋለጥ ታስቦ ሀገረ ስብከታችን የተዘጋጀውን የጡረታ ደንብ የአገልጋዮቿን እና የቤተሰባችንን ችግር የሚቀርፍ አብይ ጉዳይ ስለሆነ ከልብ የምንቀበለው መሆኑን እያረጋገጥን ይህ የጡረታ ተቀናሽ በአንድ ቋት በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እራሱን ችሎ እንዲደራጅ እየጠየቅን ለተግባራዊነቱ የበኩላችንን ድርሻ የምንወጣ መሆኑን ቃል እንገባለን፤
የቅዱስነትዎ ቡራኬ ይድረስ!
ሰኔ 23 ቀን 2009 ዓ.ም
አዲስ አበባ
ቃለ ጉባዔ ዘጋቢዎች
1.ሊቀ ብርሃናት ተክለማርያም መንገሻ                    
2.ሊቀ ኅሩያን ባዩ ተዘራ                       
3.ሊቀ ሥዩማን አምባዬ አለሙ                       
4.ሊቀ ሥዩማን ጥሩነህ ሸዋዬ                       
5.ሊቀ ሥዩማን የማነብርሃን መሲሁ                   

 
<< ጀምር < ወደኋላ 1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 ወደፊት > መጨረሻ >>

ገጽ 9 ከ 109

አድራሻ

አዲስ አበባ ፤ ኢትዮጵያ

ኢ-ሜይል: aadioces@gmail.com

ድረ ገጹ ውስጥ ይፈልጉ

ሀሳበ ባሕር(የዘመን ቁጥር)

ባሕረ ሐሳብ የዘመን መቁጠሪያ

ግጻዌ