መንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም

የምዕራብና የደቡብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ገነተ ጽጌ ቅ/ጊዮርጊስ

የምዕራብና የደቡብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔዓለም

የምዕራብና የደቡብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

መንበረ ጸባዖት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል

የምዕራብና የደቡብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ርዕሰ አድባራት መንበረ ፀሐይ እንጦጦ ማርያም

የምዕራብና የደቡብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ምስካየ ኅዙናን መድኃኔኃለም ገዳም

የምዕራብና የደቡብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም

የምዕራብና የደቡብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ደብረ ጽጌ ቅድስ ኡራኤል

የምዕራብና የደቡብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

መንበረ መንግሥት ቅ/ገብርኤል ገዳም

የምዕራብና የደቡብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ደብረ ኃይል ራጉኤል

የምዕራብና የደቡብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

http://www.addisababa.eotc.org.et/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/590538kidste_mariam.jpg http://www.addisababa.eotc.org.et/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/895720giorgis.jpg http://www.addisababa.eotc.org.et/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/903816bole_medhaniealem.jpg http://www.addisababa.eotc.org.et/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/683566trinity.jpg http://www.addisababa.eotc.org.et/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/821897entoto_mariam.jpg http://www.addisababa.eotc.org.et/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/310283meskaye_1.jpg http://www.addisababa.eotc.org.et/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/904160BEATA_MARIAM.jpg http://www.addisababa.eotc.org.et/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/578084urael.jpg http://www.addisababa.eotc.org.et/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/812647gebrie_gedam.jpg http://www.addisababa.eotc.org.et/site/components/com_gk2_photoslide/images/thumbm/681179raguel.jpg
“በዓለ ጥምቀት በኢትዮጵያ”

                                                                                                ከሊቀ ብርሃናት ኢሳይያስ ወንድምአገኘሁ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከምታከብራቸው ዘጠኝ ዓበይት በዓላት ውስጥ በየዓmቱ ጥር 11 ቀን በመላዋ ኢትዮጵያ በሚገኙት አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ በገጠርም በከተማም በታላቅ ድምቀት የሚከበረው በዓለ ጥምቀት አንዱ ነው፡፡ ይህም በዓል ከበዓላቱ ሁሉ በላይ በድምቀት የሚከበር ታላቅ በዓል ነው፡፡

የጥምቀትን በዓል አከባበር ከሁሉም በዓላት ለየት ከሚያደርጉትም ምክንያቶችና ሁኔታዎች ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡

1) ጥር 10 ቀን በዋዜማው ከተራ በሚል ስያሜ በሚታወቀው በዚሁ ዕለት ባሕረ ጥምቀት ከተዘጋጀ በኋላ በመላዋ ኢትዮጵያ በከተማም በገጠርም በመሐል አገርና በጠረፍ ጭምር ባሉት አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙት ታቦታት ሁሉ ከመንበራቸው ተነሥተው ወደተዘጋጀው ባሕረ ጥምቀት በመውረድና በተዘጋጀላቸው ድንኳን ውስጥ በማደር በዚያው በአደሩበት ድንኳን ውስጥም ማኅሌቱና ሥርዓተ ቅዳሴው ከተከናወነ በኋላ ባሕረ ጥምቀቱ ተባርኮ ሕዝበ ክርስቲያኑ ሁሉ የበረከቱ ተሳታፊ ከመሆናቸውም በላይ በዓሉ ከዋዜማው (ከከተራው) ቀን ጀምሮ ታቦታቱ ወደየአብያተ ክርስቲያናቱ ተመልሰው በመንበራቸው ላይ እስኪያርፉ ድረስ ሁለት ቀን መሉ በየባሕረ ጥምቀቱና በየመንገዱ ሁሉ በድምቀት የሚከበር በዓል በመሆኑ ነው፡፡ ይህም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለማትን የፈጠረና ሁሉንም ያስገኘ ልዑል አምላክ ሲሆን ለእኛ አርአያና ምሳሌ ይሆን ዘንድ በተዋሐደው ሥጋ ትኅትናን ገንዘብ በማድረግ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ሄዶ በአገልጋዩ በዮሐንስ መጥምቅ እጅ የመጠመቁ ምሳሌ መሆኑን ያስረዳል፡፡

2) የጥምቀትን በዓል ካህናቱ በማኅሌትና በመዝሙር፣ በቅዳሴና በልዩ ልዩ ውዳሴ፤ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በተለያዩ መዝሙራትና ሽብሸባዎች ሕዝበ ክርስቲያኑ ደግሞ ወንድ ሴት ሽማግሌና ወጣት ሕፃናትም ሳይቀሩ ሀብት ያለው አዲስ ልብስ ገዝቶ፣ ዓቅም የሌለው ደግሞ በቤት ውስጥ ያለውን አጥቦና አጽድቶ፤ ነጭ በነጭ ለብሶና አሸብርቆ እጅግ በደመቀና ባማረ ሁኔታ ታቦታቱን በማጀብ በዝማሬ፣ በሆታና በእልልታ፣ በከበሮ፣ በበገናና በእምቢልታ በታላቅ ዝግጅትና ሰልፍ በባሕረ ጥምቀቱ አካባቢና ታቦታቱ በሚያልፉባቸው መንገዶች ሁሉ በታላቅ ድምቀት የሚያከብረው በዓል መሆኑ ነው፡፡

“ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ” የሚለው ዘይቤም የሚያመለክተው ይህንኑ የጥምቀቱን በዓል ታላቅነት ነው፡፡ ነጭ በነጭ ተለብሶ የሚከበር በዓል መሆኑም በጥምቀት የሚገኘውን አዲስ ልደትና ከሐጢአት ቍራኝነት የመንፃትን ምሥጢር የሚያመለክት ነው፡፡

3)ሕዝበ ክርስቲያኑ ሁሉ በተለይም ወጣቱ ኅብረተሰብ ታቦታቱ በሚያርፉባቸው የባሕረ ጥምቀት ቦታዎች ከካህናቱ ጋር በማደርና ቀንም ታቦታቱ ወደ መንበረ ክብራቸው እንስኪመለሱ ድረስ ታቦታቱን አጅበው በመዋል፣ በልዩ ልዩ ዝማሬ፣ በጨዋታና በታላቅ ደስታ የሚያከብሩት ታላቅ በዓል ነው፡፡ በዓሉ በሁሉም አህጉረ ስብከት እጅግ በደመቀ ሁኔታ የሚከበር መሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም በደቡብ ክፍላተ ሀገር የመስቀል በዓል ከሁሉም በዓላት በላይ እንደሚከበር ሁሉ በሰሜኑ ደግሞ የጥምቀት በዓል ከሁሉም በዓላት የበለጠ እንደሚከበር ይታወቃል፡፡ በጸናው ለመናገር እንጂ የመስቀል በዓል በሰሜን፣ የጥምቀት በዓልም በደቡብ አይከበርም ማለት ግን አይደለም፡፡ የአከባበሩ ሁኔታ እንደሀገሩ የሚለያይ መሆኑን ለመግለጥ ያህል እንጂ ሁሉም በዓላት በሁሉም ቦታ እንደሚከበሩ የታወቀ ነውና፡፡በተለይም የጥር ወር በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ሰብል ተሰብስቦ የሚያበቃበትና ምርት የሚታፈስበት ከመሆኑም በላይ ለገበሬው ኅብረተሰብ የዕረፍት ጊዜ ስለሆነ በዚያውም ላይ ምርቱ በጎተራ ስለሚኖር በዓሉ በዘፈን በጨዋታ ብቻ ሳይሆን በመብል በመጠጥ፣ በተድላና በደስታ የሚከበር በዓል በመሆኑ ይህ በዓል በካህናትና በምእመናን ዘንድ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ዘንድ እጅግ ተወዳጅና ተናፋቂ፤ የሁሉንም ቀልብ የሚያስብና የሚማርክ ነው፡፡ በመሆኑም ፆታና ዕድሜ ሳይለይ ሁሉም በታላቅ ስሜትና ፍቅር ያከብረዋል፡፡

የጥምቀት በዓል በተለይም በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ያሉ ወጣቶች ሁሉ ከእረኝነትና ከመሳሰሉት አድካሚ ሥራዎች ሁሉ ነፃ ሆነው የሚዝናኑበትና የወጣትነት ስሜታቸውን በዘፈን፣ በጭፈራ በእስክስታና በጨዋታ የሚገልጡበትና የኑሮ ጓደኛ የምትሆናቸውንም ኮረዳ የሚመርጡበትና የሚያጩበት ወቅትና ጊዜ ሆኖ ቆይቶአል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በተለይ የከተማው ወጣቶች በዓሉን የሚያከብሩት በእስክስታና በዘፈን በጨዋታ ሳይሆን አብዛኛዎቹ መዝሙር እየዘመሩና እያሸበሸቡ እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑበት በዓል እየሆነ መምጣቱ እጅግ የሚያስደስትና ዓላማውንም የጠበቀ ሆኖአል ማለት ይቻላል፡፡

የበዓሉ ታላቅነት መገለጥ ያለበትም በተድላ በደስታው በዘፈን በጨዋታው ሳይሆን በውስጡ ያለውን ጥልቅና ረቂቅ ምሥጢር በመመርመርና በማስታወስ ሊሆን ይገባል፡፡ ይኸውም፡ -

1. ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእደ ዮሐንስ፣ በማየ ዮርዳኖስ በተጠመቀ ጊዜ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል እግዚአብሔር አብ በደመና ሆኖ “ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር ወሎቱ ስምዕዎ” ማለት “በእሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው ቃሉን ስሙት” እያለ ሲናገር በግልጥ ተሰምቶአል፡፡

2. አሁንም ከሦስቱ አካላ አንዱ አካል እግዚአብሔር ወልድ (ኢየሱስ ክርስቶስ) በለበሰው (በተዋሐዳው) ሥጋ በማየ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ በግልጥ እየታየ ተጠምቆአል፡፡

3. ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላም ሦስተኛው አካል እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ከሰማይ ሲወርድና በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራስ ላይ ሲያርፍ በግልጥ ታይቶአል፡፡ በዚህም ምክንያት የጥምቀት በዓል የሚከበርበት ወቅት ዘመነ አስተርእዮ በመባል ይታወቃል፡፡ አስተርእዮ ማለትም መገለጥ ማለት ነው፡፡

ስለዚህ በዓለ ጥምቀት የቅድስት ሥላሴ አንድነትና ሦስትነት የታወቀበት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ እውነተኛ አምላክ መሆኑ የተመሰከረበት ዕለት ስለሆነ ይህ ረቂቅ ምሥጢር የበዓሉን ታላቅነት ያረጋግጣል፡፡ (ማቴ. 3÷13-17፤ ማር. 1÷9-11፤ ሉቃ. 3÷21)፡፡

4. በዓለ ጥምቀት “አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ፣ ሄዋን አመቱ ለዲያብሎስ” ተብሎ በዲያብሎስ አስገዳጅነት ተፈርሞ የነበረው የአዳምና ሄዋን የዕዳ ደብዳቤ የተደመሰሰበትና የሰው ልጆች ሁሉ ከሰይጣን ባርነት ነፃ የወጡበት የነፃነት መታሰቢያ በዓል በመሆኑና ክርስቲያኖች ሁሉ በጥምቀት በሚገኝ ዳግም ልደት የእግዚአብሔር ልጆች መሆናቸው የተረጋገጠ ስለሆነ በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ ስም ለተጠመቁ ክርስቲያኖች ሁሉ የዳግም ልደታቸው መታሰቢያ በዓል ነው፡፡ በመሆኑም በዓለ ጥምቀት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ዘንድ በታላቅ ክብርና ከሁሉም በዓላት በላይ በሆነ ድምቀት ሲከበር ኖሮአል ወደፊትም በዚሁ ይቀጥላል፡፡

ማጠቃለያ

እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሥርዓትና ትውፊት ባሕረ ጥምቀቱ ተባርኮ ምእመናን በተባረከው ውኃ የሚረጩትና የሚጠመቁት ጥምቀትን ለመድገምና እንደገና መንፈሳዊ ልጅነትን ለማግኘት ወይም ለማደስ ሳይሆን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ጥምቀት በሚታይ ምሳሌ ለመግለጥና በረከት ለማግኘት መሆኑን፤ እንዲሁም ታቦታቱ ወደ ባሕረ ጥምቀቱ መውረዳቸውና ካህናቱና ሕዝቡም ታቦታተ ሕጉን አክብረው ወደ የባሕረ ጥምቀቱ መውረዳቸው ከላይ እንደተገለጠው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ሂዶ በእደ ዮሐንስ በማየ ዮርዳኖስ መጠመቁን የሚያስረዳ ታላቅ ምሳሌና እውነተኛ የመታሰቢያ በዓል መሆኑን ያመለክታልና የበዓሉን ድምቀት ብቻ ሳይሆን ምሥጢሩን በጥልቀት ልንመረምረውና ልብ ልንለው ይገባል፡፡

 

 
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ የ2010 ዓ.ም የልደት በዓልን አስመልክተው መልእክት አስተላለፉ

pp009

ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በእንተ በዓለ ልደቱ ለእግዚእነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ሎቱ ስብሐት!!

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!

-በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፤

-ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤

-የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤

-በሕመም ምክንያት በየፀበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤

-እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤

በልደቱ፣ ፍጻሜ የሌለው ሰላምን ያበሠረን፤ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ 

እንኳን ለብርሃነ ልደቱ በሰላም አደረሳችሁ!!

ወአልቦ ማኅለቅት ለሰላሙ፤ለሰላሙ ፍጻሜ የለውም፤(ኢሳ.9:7)

በዚህም ዓለም ይሁን በወዲያኛው ዓለም፣ በግዙፋኑም ይሁን በረቂቃኑ ፣ በኃያላኑም ይሁን በድኩማኑ፣ በሀብታሙም ይሁን በድሀው በአጠቃላይ በተንቀሳቃሹ ፍጡር ሀልዎት ውስጥ መቀጠል የሰላም አስፈላጊነት ከሌላው ጸጋ ሁሉ የላቀ ነው፣ሰላም ካለ ሌላው ሁሉ የትም አያመልጥም፤ ሰላም ካለ ድህነቱም ይቀረፋል፣ ጕድለቱም ይሟላል፣ልማቱም ይስፋፋል፣ዕድገቱም ይረጋገጣል፣ ፍትሕ ርትዕም ይሰፍናል፤ ወንድማማችነቱም ይጸናል፤ አንድነቱም ይረጋገጣል፣ ሰላም በዕለት ተዕለት ሥራችንና በምድራዊ ሕይወታችን በሚሆን ገጠመኝ ብቻ ሳይሆን ከፈጣሪ ጋር በሚኖረን ግንኙነትም ዓቢይ ትርጉም አለው፤ ለሰላም ህልውና መጠበቅ ትልቅ ስፍራ ያለው ፈጣሬ ፍጥረታት እግዚአብሔር የሰላም አምላክ ነውና ፍጡራን በሰላም እንዲኖሩ መለኮታዊ መልእክቱን ማስተላለፍ ብቻ ሳይሆን መሥዋዕትነትም ከፍሎበታል፤ ለዚህም ዋናው ማስረጃችን የአምላክ ሰው መሆንና በሰው አካል በዚህ ዓለም ተገልጾ ስለ ሰላም የሰጠው ጥልቅ ትምህርት ነው፡፡

በትምህርትም በተግባርም እንደምንገነዘበው በሰዎች ግብታዊ ድርጊትም ሆነ፣ ሆን ተብሎ በሚፈጸም ማስተዋል የጎደለው ክንዋኔ ሰላም ሊደፈርስ ይችላል፤ በአንጻሩ ሰዎች በማስተዋል፣ አርቆ በማሰብና በብዝኃ ትዕግሥት በሚመሩት ጤናማ ሕይወት ሰላም ሊፀና ሊሰፋና ወደ ላቀ ደረጃ ሊሸጋገር ይችላል፡፡

በየዓመቱ የምናከብረው የጌታችን በዓለ ልደት ይህንን ሐቅ ቊልጭ አድርጎ ያሳየናል፣የበዓሉ ታሪካዊ መነሻ እንደሚነግረን የቀደሙ ወላጆቻችን ማለትም አዳምና ሔዋን ለሕይወታቸው ጠቃሚ የሆነው ሕገ እግዚአብሔር በውል ተነግሮአቸው እያለ በጎን የመጣውን የጠላት ምክር ተቀብለውና ሆን ብለው ትእዛዙን ስለተዳፈሩ ሰላም ሊደፈርስባቸው ችሏል፡፡

በመሆኑም ያደፈረሱት ሰላም ቅጣትን አስፈርዶ ዕርቃናቸውን አስቀራቸው፤ በሐፍረት አከናነባቸው፤ መሠወር ባይችሉም መሸሸግንና መሸፋፈንን እንደ አማራጭ ዘዴ ሊጠቀሙ ሞከሩ፣ እውነተኛው ዳኛ ለምን ሰላሙን አደፈረሳችሁ ብሎ በጠየቃቸው ጊዜ ምክንያቶችን ቢደረድሩም በቀጥተኛው ሕግ ፊት ማምለጫ አላገኙም፤ ምክንያቱም ሰላምን አደፍርሰው ሞትን እንዳይጎትቱ ማስጠንቀቂያው ከበቂ በላይ በግልፅ ተነግሮአቸው ነበርና ነው፡፡

የጉዳቱ መጠን በዚህም አላበቃም፣ በእነሱ ጠንቅ ዘራቸውም  ተቀጣ፣ በምድር ላይ የሚገኙ ፍጥረታትና ምድሪቱም ራስዋ በከባድ መርገም ተቀጣች፤ በዚህም ምክንያት የሰው ሁለንተናዊ ሕይወት ዘላቂና እውነተኛ ሰላምዋ የሆነው እግዚአብሔርን አጥታ ለአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዓመታት በተሳሳተ አምልኮና በተመሰቃቀለ ህላዌ እየታመሰች፣ ሞትና መቃብርም ያለማቋረጥ እየተናጠቋት፣ እግዚአብሔር ያዘጋጀላት ብሩህ ዓለም ተዘግቶባት በጨለማው ዓለም ውስጥ ስትማቅቅ ኑራለች፤ የዚህ ሁሉ መከራ መንሥኤው አንድና አንድ ብቻ ነበር፤ እሱም የሰላሙ ኃይል እንደዋዛ ከእጅዋ ማምለጡ ነው፡፡

 የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት

ከሦስቱ አካላት አንዱ የሆነው እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ ሰው ሆኖ የተወለደውና በዚህ ዓለም የተገለፀው ለሰላሙ ፍጻሜ የለውም ብሎ በቅዱሳን ነቢያቱ ያናገረውን የማይታጠፍ ቃሉን ለመፈጸም ነው፡፡

ቅዱሳን መላእክትም በጌታችን ዕለተ ልደት በቤተ ልሔም ተገኝተው እግዚአብሔርና ሰው በመገናኘታቸው ሰላም በምድር ሆነ፤ ይህም በእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ተከናወነ ብለው በመዘመር፣እረኞችም የመዝሙሩ ተጋሪ በመሆን ያሳዩት አንድነት የተነገረው ሰላም መፈጸሙን ያረጋገጠ ነበር ፡፡

በእርግጥም በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ሰላም መፈጠሩን ለመረዳት እግዚአብሔር ሰው ሆኖ ከተገለጠበት ክሥተት የበለጠ ሌላ ማረጋገጫ ሊገኝ አይችልም፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዕለተ ልደቱ እስከ መዋዕለ ዕርገቱ ድረስ በፈጸመው የቤዛነት ተግባር፣ የደፈረሰውን ሰላም እንደገና በመመለስ በሰውና በሰው፣በእግዚአብሔርና በሰው፣በመላእክትና በሰው መካከል የነበረውን የጥል ግድግዳ በመናድ ሰላማችንና አንድነታችንን እውን አድርጎአል፤ ከጨለማው ዓለም ብሩህ ወደሆነው ዓለም እንደገና መልሶናል፤ ይህ እግዚአብሔር በምሕረቱ ብዛት ለሰው ልጅ ያጎናጸፈው ትልቁ፣ ዘላቂውና ዘላለማዊው ሰላም ነው፤ እሱም እኔ  ሰላሜን እሰጣችኋሁ፤ እኔ የምሰጠው ሰላም ዓለም እንደሚሰጠው ያለ አይደለም  ብሎ የተናገረለት ሰማያዊ፣ ዘላለማዊና ሳይቀለበስ ለዘላለሙ ጸንቶ የሚኖረው፣ ከእርሱና ከፍጡራን ሁሉ ጋር የሚሆነውና መጨረሻ የሌለው  ሰላም ይህ በልደቱ ተጀምሮ በዳግም ምጽአቱ የሚደመደመው ታላቁ ሰላም ነው ፡፡

ይሁን እንጂ በምድርም ቢሆን ሰው ዛሬውኑ አዳምጦ፣ አስተውሎ፣ አምኖና ተቀብሎ በተግባር ቢያውለው ጌታችን የሰላም ትምህርቱን ለክርክር በማይዳርግ መልኩ ሰጥቶአል፤ እርሱም  ‹‹ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ  እናንተም እንደዚሁ አድርጉላቸው፤ በራስህ ላይ ሊደረግብህ የማትሻውን በባልንጀራህ ላይ አታድርግ፤ ባልንጀራህን እንደራስህ አድርገህ ውደድ›› የሚለው እውነተኛ የሰላም መንገድ ነው፤ ዛሬም ይህን ቃሉን ተቀብለን በተግባር ብንፈጽም ሰላማችን አስተማማኝና ዘላቂ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት፡-

ሰላም ማለት የእግዚአብሔር ሕግ ማለት ነው፤ ሰላምን የፈጠረ፤ ከማንም አስቀድሞ ስለ ሰላም ያስተማረና አሰምቶ የተናገረ፤ ደጋግሞም ያስጠነቀቀ እግዚአብሔር ነው፤ቃሌን ብታደምጥ ብትጠብቀውም ሰላምህ እንደማያቋርጥ ወንዝ ይጎርፋል ያለ እርሱ ነው ፡፡

ይህም ማለት ዘላቂና ፍጹም ሰላም ያለው በእግዚአብሔር ሕግ ውስጥ መሆኑን ያሳያል፤ ይህንን ሕገ ሰላም አውቀን በታላቅ አክብሮትና ምስጋና ስንቀበለው ሰላማችን ዘላቂና አስተማማኝ ይሆናል ማለት ነው፤ ዘላቂና ፍጹም የሆነ የእግዚአብሔር ሰላም በአንድ አጭር ዐረፍተ ነገር ባልንጀራህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ›› ተብሎ ተነግሮናል፡፡

ይህ ዓቢይና መለኮታዊ የሰላም ሕግ ከተከበረ መለያየት፣ መጣላት፣ መጨካከን፣ መገዳደል፣ በየት መግቢያ ያገኛል? እግዚአብሔር የሚፈልገው ሰላም ምን ዓይነት እንደሆነ መመዘኛውና መለኪያው እኛ ራሳችንን የምንወደው ያህል ወንድሞቻችንንና እኅቶቻችንን መውደድ ነው፤ በዚህ ፍጹምና አምላካዊ ሕግ በእግዚአብሔር መልክና አምሳል የተፈጠረውን ሰው ሁሉ እንደራሳችን አድርገን እንድንወድ ታዘናል፤ እኛም አምነን ተቀብለናል፤ ይህንን የእግዚአብሔር ድምፅ ያልሰማ ሰው በሀገራችን በኢትዮጵያም ሆነ በሌላው ክፍለ ዓለም ይኖራል ብለን አንገምትም፤ነገር ግን የቀደሙ ወላጆቻችን የእግዚአብሔርን ድምፅ ወደጎን ትተው በመጓዛቸው እንደተጎዱ፣ ዛሬም የሰው ልጅ ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ የሚለውን ድምፅ ቸል በማለት አጥፍቶ በሚጠፋ ቊሳቊስ እየተጣላ የሰላሙን ጭላንጭል በገዛ ራሱ እያጨለመው ይገኛል፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት

ሰላምን ለመጎናጸፍ ሁለት ዐረፍተ ነገሮችን መቀበልና ዘወትር ስለነሱ መዘመር በቂያችን ነው፣ እነርሱም እግዚአብሔር አምላክህን በሁለመናህ ውደድ፤ ባልንጀራህንም እንደራስህ አድርገህ ውደድ የሚሉት ናቸው፡፡

ይህች ፍቅር የእግዚአብሔር ጸጋ ሆና የተሰጠችን፣ ሌላ አማራጭና ተፎካካሪ የሌላት ፣ ኅሊናን ሁሉ የምትረታ ናት፣ምንጩ እግዚአብሔር የሆነ የሰላምና  የፍቅር ኃይል  ድንበር ፣ ወንዝ ፣ ቋንቋ  አይገድበውም፤ በመሆኑም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሙሉእ ሰላምን የሚሰጠው እግዚአብሔር ስለሆነ፣ አሁኑኑ እግዚአብሔርን ያድምጥ፤ ያዳመጠ ዕለታ ‹‹ወንድምህን እንደራስህ አድርገህ ውደድ፣ ወንድምህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ፣ ወንድምህን እንደራስህ አድርገህ ውደድ›› የሚል ቃል በተደጋጋሚ ከአምላኩ አንደበት ይሰማል፣ እርሱን ተቀብሎ በተግባር ሲያውል እግዚአብሔር አምላክህን በሁለመናህ ውደድ የሚለው ፍቅር በሕይወቱ ይገለጻል፤ በእርሱም ፍጹም ሰላም ያገኛል፡፡ ከዚህ አኳያ በዓለ ልደቱን ስናከብር እርሱ እንደራራልን እኛም የእርሱን ፈለግ ተከትለን የተራቡትን፣ የተጠሙትን፣ የታረዙትንና የተፈናቀሉትን በመርዳት እንዲሁም ቀኑ የሁሉም ወገን የደስታ ቀን እንዲሆን በማድረግ ልናከብር ይገባል፡፡

በመጨረሻም

ጅብ በቀደደው እንደተባለው ዘላቂ የሆነ የጋራ ጥቅማችንን ሳናይ በምንፈጥረው ስሜታዊ ክፍተት ተጠቅመው ታላቅነታችንንና ዕድገታችንን የማይሹ ኃይሎች ከሕዳሴው አጀንዳችን እንዳያናውጡን ኢትዮያውያን የሆን ሁላችን፣ ከሃይማኖታችን ያገኘነውን ቅዱሱና ሰላማዊው የአንድነት ሀብታችንን ጠብቀን፣ ቂምንና በቀልን አርቀን የውስጣችንን ክፍተት ራሳችን በራሳችን አርመን በአንድነት በሰላምና ፍጹም በሆነ ወንድማዊ ፍቅር ቀጥ ብለን በመቆም ወደፊት እንድንቀጥል በእግዚአብሔር ስም መንፈሳዊመልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡

መልካም የልደት በዓል ያድርግልን

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ይባርክ ይቀድስ፡፡

‹‹ወስብሐት ለእግዚአብሔር››

አሜን

አባ ማትያስ ቀዳማዊ፣

ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣

ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣

ታኅሣሥ ፳ ቀን ፳፻ወ ዓ.ም

አዲስ አበባ ኢትዮጵያ ፤

 

 
"ኖላዊሆሙ ለእስራኤል አጽምእ"(የእስራኤል ጠባቂ ሆይ አድምጥ)

                                                                                                                      በመ/ር ሣህሉ አድማሱ

4521

በቤተክርስቲያናችን የቃለ እግዚአብሔር አሰጣጥ መሠረት ከብርሃን ቀጥሎ ያለው ሳምንት ኖላዊ ተብሎ ተሰይሟል፡፡

ኖላዊ ተብሎ  በሚጠራው ሰንበት "ኖላዊ  ዘመጽአ…" የሚለው የቅዱስ ያሬድ የዜማ ድርሰት በሌሊት  የአገልግሎት ክፍለ ሰዓት በሊቃውንቱ ሲዘመር ያድራል፡፡ በጧቱ በሥርዓተ  ቅዳሴ ወቅት (ዕብ.13÷16)፣ (1ጴ 2÷21)፣ (የሐ.10÷36-43 በዲያቆናትና  በካህኑ  በንባብ ይቀርባል፡፡ የእስራኤል ጠባቂ ሆይ አድምጥ፣ዮሴፍን እንደመንጋ  የምትመራ፣ በኪሩቤል  ላይ የምትቀመጥ ተገለጥ የሚለው የዳዊት መዝሙር (መዝ 79÷1) በዲያቆኑ በዜማ ይቀርባል፡፡ (ዮሐ 10÷1-22) በካህኑ በዜማ ይቀርባል፡፡ ቃሉም እንዲህ ይነበባል፡፡ 

"አማን አማን  እብለክሙ ዘኢቦአ እነተ  አንቀጽ ውስተ አጸደ አባግዕ ወአርገ እንተካልእ ገጽሰራቂ ወፈያት ወጉህልያ ውእቱ"

"እውነት እውነት እላችኋለሁ ወደ በጎች በረት በበሩ የማይገባ በሌላ መንገድ ግን የሚወጣ እርሱ ሌባ ወንበዴም ነው፡፡ በበሩ የሚገባ ግን የበጎች  እረኛ ነው፡፡  ለእርሱ  በረኛው  ይከፍትለታል፡፡ በጎቹም ድምጹን ይሰሙታል፡፡የራሱንም በጎች በየስማቸው ጠርቶ  ይወስዳቸዋል፡ ፡የራሱንም ሁሉ ካወጣቸው በኋላ በፊታቸው ይሄዳል፡፡ በጎቹም ድምፁን ያውቃሉና ይከተሉታል፡፡ ከሌላው ግን ይሸሻሉ እንጂ አይከተሉትም፡፡ የሌሎችን ድምፅ  አያውቁምና፡፡ .. እኔ የበጎች  በር  ነኝ….በሩ እኔ ነኝ በእኔ የሚገባ  ይድናል፡፡

….መልካም እረኛ እኔ ነኝ፡፡ መልካም እረኛ ነፍሱን ስለበጎቹ ያኖራል፡፡ እረኛ ያልሆነው በጎቹ የእርሱ ያልሆኑ ሞያተኛ ግን ተኩላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ  ይሸሻል፡፡

በግ

በግ ሥጋው  ለመስዋዕትነትና ለምግብ፣ ጠጉሩና ቆዳው ደግሞ ለልብስ  የሚሆን  የዋህ የቤት እንስሳ ነው (ዘፍ 4÷2) (ዘሌ 22÷19) (ዘፀ 14÷13) በግ በተለይ  ለፋሲካ መስዋዕት  ይታረድ ነበር (ዘፀ 12÷3) ስለዚህ ክርስቶስ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአበሔር  በግ ተብሏል፡፡ (ዮሐ1÷29) (ራዕ 5÷6)በግ ንጹሕና የማይጎዳ የዋህ እንስሳ ስለሆነ ሐሰተኞች  የዋህ  ለመምሰል  የበግ  ለምድ  በሚለብሱ  ተመስለዋል፡፡ (ማቴ 7÷15)በጎች ክርስቶስን የሚከተሉ ምዕመናን ምሳሌ ናቸው፡፡(ማቴ 25÷33)

እረኛ

 በጎችንና ፍየሎችን ከብቶችንም የሚያሰማራ እረኛ ተብሎ ይጠራል፡፡ (መዝ 23÷2)እረኛ  የጠፋውን  ይፈልጋል፡፡ (ሉቃ 15÷3) ከአውሬዎችም ይጠብቃል(1ሳሙ 17÷34)

እረኛ ኃላፊነት ላለባቸው ሁሉ ምሳሌ ነውና፣ ሕዝብን የማይጠብቁ ባለስልጣኖች ከባድ  ፍርድ  ይጠብቃቸዋል፡፡ (ኤር23÷1)፣ (ሕዝ34÷1)

በበሉይ ኪዳን ስለ እግዚአብሔር እረኝነት የተነገረው ሁሉ በአዲስ ኪዳን ለክርስቶስ  ተነግሯል፡፡ ይህም ክርስቶስ ራሱ እግዚአብሔር መሆኑን ያመለክታል፡፡ ኢየሱስ ፈሪሳውያን ዕውር መሆናቸውን ተናግሮ እንደጨረሰ ስለመልካም እረኛ ማስተማር ጀመረ፡፡ በብሉይ ኪዳን እንደተጻፈው የአይሁድ መሪዎች የእስራኤል ጠባቂዎች እረኞች ናቸው፡፡

ይሁን እንጂ መሪዎች ይህን ሀላፊነት መወጣት አልቻሉም፡፡ ዕውሮችና ምንም ነገር የማያውቁ ሆኑ (ኢሳ 56÷9)ሐሰተኞች፣ በበጎች በር የማይገቡ፣ ሌቦችና ወንበዴዎች ሆኑ፡፡

እውነተኛ እረኛ የሆነው ከርስቶስ ሁል ጊዜ በበሩ  ይገባል፡፡ በብሉይ ኪዳን እራሱ እግዚአብሔር የእስራኤል እረኛ እንደሆነ ተነግሯል፡፡ (መዝ 23÷1) ፣ (ሕዝ34÷15) ኢየሱስ ክርስቶስ እረኛችን ነው፡፡ እርሱም ከእርሱ በታች ሌሎች እረኞችን  ሾሟል፡፡ (የሐ 20፣17)ክርስቶስ ሕይወቱን ለበጎች አሳልፎ የሰጠ መልካም እረኛ ነው፡፡

ቅጥረኛ እረኛ ግን ተኩላ ሲመጣ በጎቹን ጥሎ ይሸሻል፡፡ በየትኛውም ዘመን ከቤተክርስቲያን መሪዎች መካከል ቅጥረኛ የሆኑ እረኞች አሉ፡፡ እነዚህ እረኞች መንጋውን  አያስቀድሙም፡፡ አንድ ችግር በመጣ ጊዜ መንጋውን በትነው  ይሸሻሉ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በጎቹን ያውቃል ፣ ደግሞም በጎቹን ይወዳል፡፡ በመሆኑም ስለበጎቹ ሕይወቱን አሳልፎ ሰጥቷል፡፡

 

 

 
<< ጀምር < ወደኋላ 1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 ወደፊት > መጨረሻ >>

ገጽ 1 ከ 109

አድራሻ

አዲስ አበባ ፤ ኢትዮጵያ

ኢ-ሜይል: aadioces@gmail.com

ድረ ገጹ ውስጥ ይፈልጉ

ሀሳበ ባሕር(የዘመን ቁጥር)

ባሕረ ሐሳብ የዘመን መቁጠሪያ

ግጻዌ